የሲዳማ ባሕላዊ ሐይማኖት


የሲዳማ ባህላዊ ሐይማኖት(በኖሞናኖቶ)

ሲዳማኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መካከል አንዱ ሲሆን፡ ቀድሞ የሲዳሞ ክፍለ አገር ይባል በነበረው እና በአሁኑ ጊዜ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት አካል በሆነው ሲዳማ ዞን ውስጥ የሚገኝ ህዝብ ነው። ህዝቡ ከሲዳማ ዞን ውጪ በአጎራባቹ የኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች ውስጥ ይኖራል። የህዝብ ብዛቱም ከአራት ሚሊዮን በላይ እንደሆነ የተለያዩ ዶክመንቶች ያመለክታሉ።

ሲዳማዎች የአፍሮ - እስያቲክ ግንድ ካላቸው እና በሰሜን አፍሪካ፣ በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ እስያ ከሚነገሩ 375 ቋንቋዎች አንዱ የሆነ እና ከኩሽ ወይም ከኩሺቲክ የቋንቋ ቤተሰብ የሚመደብ ቋንቋ ይናገራሉ። ከቋንቋቸው ባሻገር እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ሁሉ የራሳቸው የሆነ ባህል፣ እምነት፣ አስተዳደራዊ ስርዓት፣ መገበያያ ገንዘብ፣ የጊዜ እና ዘመን አቆጣጠር ስርዓት እና ሌሎች ማህበራዊ እሴቶች ያሉት ህዝብ ነው።

ሲዳማዎች ለዘመናት ከአባት ወደ ልጅ እያወረሱ ካቆዩት እሴቶቻቸው መካከል ባህላዊ ሐይማኖት ይገኝበታል። በሐይማኖቱ መሰረት ሲዳማዎች በማጋኖ ( አምላክ ወይም እግዚአብሔር) ያምናሉ። ማጋኖ ፣ ሐላሌ ( እውነት) እና አካካ ( አባቶች፣ አያቶች፣ ቅድመ አያቶች) የእምነታቸው ምሰሶዎች ናቸው። በእነዚህ ሶስቱ ምሰሶዎች ላይ እና በእምነቱ አጠቃላይ ጽንሰ ሐሳብ ላይ አንዳንድ ሀሳቦችን ከማንሳት በፊት ስለአካኮዎች ወይም አባቶች፣ አያቶች፣ ቅድመ አያቶች ወይም ስለሲዳማ ጎሳዎች ትንሽ ልበል።

ሲዳማዎች ከመካከለኛው ምስራቅ ባህርን ተሻግረው ወደ አፍሪካ ቀንድ መምጣታቸውን፣ በመጀመሪያ «ዳዋ» 1 ከሚባል ቦታ ላይ መስፈራቸውን ቀጥሎም በባሌ አድርገው አሁን ወዳሉበት አከባቢ መምጣታቸውን የብሔሩ ሽማግሌዎች ይተርካሉ። በትረካቸውም አሁን ወዳሉበት አከባቢ እንዲመጡ ያደረጋቸው የአባታቸው ጉዛዜ መሆኑን ይናገራሉ። እንደሽማግሌዎቹ ገለፃ፡ ሲዳማዎች የሁለት አባቶች ልጆች ሲሆኑ፡ ቡሼ የሚባለው አንደኛው አባታቸው ሲሞት ከመቃራቸው ጉድጓድ የሚወጣው አፈር ከተቀበሩ በሃላ ሲመለስ ከመሬት ከፍ ወይም ዝቅ ከሚል ቦታ እንዳይቀብራቸው በተናዘዙት መሰረት የአባታቸውን ሬሳ በተለያዩ አካባቢዎች እና ቦታዎች ለመቅበር ሞክረው ስላልተሳካላቸው መጀመሪያ ከሰፈሩበት አካባቢ ተነስተው በባሌ አድርገው እግሬ መንገዳቸውን የአባታቸውን ሬሳ እየቀበሩ እያወጡ ዛሬ ወዳሉበት አከባቢ መጥተዋል። በአከባቢውም የአባታቸውን ሬሳ ሲቀብሩ በተናዘዙት መሰረት ከመቃብር ጉድጓድ የወጣው አፈር ወደ መቃብሩ ሲመለስ ከመሬት እኩል በመሆኑ የአባታቸው የመጨረሻ የመቃብር ቦታ ሆነ። ከአባታቸው የመቃብር አከባቢ መራቅ ያልፈለጉት ሲዳማዎችም በአከባቢው ሰፍረው እስከአሁን ይኖራሉ።

እንግዲህ ስለሲዳማዎች አባት ኑዛዜ አፍጻጸም ያለምክንያት አይደለም ያነሳሁት፡ በብሔሩ ባህላዊ ሐይማኖት መሰረት የእርሱ የመቃብር ቦታ እና ሌሎች መሰል የጎሳ አባቶች መቃብሮች በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ስላላቸው ነው። ወደታች በስፋት አነሳዋለሁ።

ለባህላዊ ሐይማኖቱ መሰረት የሆነው ሌላው ማጋኖ ነው። ከላይ እንዳነሳሁት የሐይማኖቱ ተከታዮች በማጋኖ ( አምላክ ወይም እግዚአብሔር ) ያምናሉ። ለማጋኖ፤ ካላቃ (ፈጣሪ)፣ ካሊቃ (ሃያል ሁሉን ቻይ) እና ሐላላንቾ (እውነተኛ) በማለት ሶስት ገጽታዎችን ይሰጡታል። ከዚህም በተጨማሪ ማጋኖ፤ እውነተኛ ወዳጅ፣ ለልጆቹ የሚሳሳ፣ የሚራራ፣ ሲያጠፉ የሚገጽጽ፣ ሀጢኣያታቸው የሚምር ሩህሩህ አባት ነው ይላሉ።

በሐይማኖቱ ማጋኖ አምሳያ የለውም። በአምሳሉ የተቀረጹ ወይም የቆሙ ወይም መልኩን የሚያሳዩ ቁሶች የሏቸውም፤ ነገር ግን ቀን በቀን ከመሃከላቸው እንደሚገኝ ያምናሉ። ስሙ በራሱ የሚፈራ እና የሚከበር በመሆኑ ለመልካም ስራ ካልሆነ ለክፉ ተግባራት ማለትም ለማታለሊያነት፣ ውሸት ለመናገር፣ ወዘተ አይጠራም። ለክፋት ስሙን ማንሳት ወይም መጥራት ማጋኖን ያስቆጣል ተብሎ ይታመናል።

ማጋኖ የሰውን ልጅ ከአፈር ፈጥሮ ትንፋሹን ከሰጠው በኋላ ወደ ሰማይ አረገ። ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ከፈጠው የሰው ልጅ ጋር በሐላሌ አማካይነት ይገናኝ ነበር። ሐላሌም በሰው እና በካሊቃ መካከል እንደድልድይ ሆነ ስለ ሰው ልጅ ያማልዳል ነበር።

የእምነቱ ተከታዮች እንደምሉት ከሆነ፤ ሐላሌ ሲዳማዎች ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት ብቸኛው ድልድይ በመሆኑ ታላቅ ክብር እና ዋጋ ይሰጡት ነበር። በመጀመሪያ ላይ ሐላሌ በአይን የምታይና በእጅ የምዳሰስ፤ ሰዎች በሚያሹት ወቅት በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ የሚገኝ ብሎም በሰው ልጆች መካከል የሚመላለስ ነበር።

ሐላሌ ለሲዳማዎች ቅርብ ከመሆኑ እና ሲዳማዎችም ለሐላሌ ካላቸው ክብር የተነሳ በእርሱ ይተዳደሩ ነበር፤ ሐላሌም ሲዳማን ያስተዳድር ነበር። ነገር ግን ከብዙ ዓመታት በኋላ የሰው ልጆች በክፋት፣ ጥላቻ፣ ተንኮል ፣ ክህደት እና በሌሎች ክፉ ተግባራት እየተሰማሩ የፈጣሪን ትዕዛዛት እየጣሱ ሲመጡ፤ ሐላሌ ከመሃከላቸው መመላለስን እና ማስተዳደሪን ትቶ ወደ ፈጣሪ ወይም ካሊቃ ዘንድ ለመሄድ ተነሳ።

ሐላሌ ከመካከላቸው እንደማይኖር እና ጥሏቸው ወደ ካሊቃ (ማጋኖ) እንደሚሄድ የተረዱ እና ከእንግዲህ ከፈጣሪ ጋር እንደት ሆኖ እንደምገናኙ ያልተረዱት የእምነቱ ተከታዮች ሐላሌ ለማን ጥሏቸው እንደሚሄድ ጠየቁት። ሐላሌም ከእንግዲህ ከካሊቃ ጋር የምትገናኙት በአባቶቻችሁ በኩል ነው። አባቶቻችሁ ከፈጣሪ ጋር ያገናኟችሃል፣ ስለእናንተ ፈጣሪን ይማለዱላችሃል ብሏቸው ወደ ሰማይ አረገ።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሐይማኖቱ ተከታዮች በሞት የተለዮቸው አባቶቻቸው፣ አያቶቻቸው፣ ቅድመ አያቶቻቸው ከማጋኖ ጋር ይኖራሉ ብለው አመኑ፤ ከማመንም በላይ ከማጋኖ ጋር ለመገናኘት አባቶቻቸውን መጠቀም ጀመሩ።

በእምነቱ ፊልስፊና መሰረት «እኔ ከእኔ በላይ አባቴ ፣ ከአባቴ በላይ ቀደሚት አባቶቼ፣ ከቀደሚት አባቶቼ በላይ ካሊቃ (ማጋኖ)» ተብሎ ይታመናል። ከእምነቱ ጋር በተያያዘ እና በሌሎች ማህበራዊ ምክንያቶች የተነሳ ሲዳማዎች ለአባቶች እና ለአረጓውያን የተለየ አክብሮት አላቸው።

እንግዲህ ሐላሌ ወደ ካሊቃ ካረገበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አባቶች የእምነቱን ተከታዮች ከፈጣሪ ያገናኛሉ፣ ያስታርቃሉ፣ ስለእነርሱ ይማለዳሉ።ከዚህም ባሻገር የማህበረሰቡ ስነ ምግባር ወይም የግብረገብነት እና ሐይማኖታዊ ሕግጋት መከበራቸውን ይቆጣጠራሉ።

የአባቶቻቸው የመቃብር ቦታም የእምነቱ ስነስርዓት ማካሄጃ ቦታ ሆነው ያገለግላሉ። ከላይ ከመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት፤ የሲዳማ ጎሳዎች አባቶች በተለይ ሁለቱ የሲዳማ ዘር የተነሳባቸው አባቶች መቃብር ቦታዎች በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ቦታዎች ናቸው።

በሲዳምኛ ሞጎ ተብለው የሚታወቁት የአባቶች እና ቅድመ አባቶች ወይም የአካኮች መቃብሮች፤ ታጥረው በጥንቃቄና በንፅህና የተያዙ፣ የእምነቱ ተከታዮች ፈጣሪውን ለማምለክ የሚሰባሰብባቸው፣ እንዲሁም ፈጣሪን መማጸኛ መስዋዕቶችን የሚያቀርቡበት ቅዱስ ስፍራ ነው።

በእነዚህ በትላልቅ ዛፎች በተሞሉ 2 ቅዱስ ስፍራዎች የእምነቱ መሪዎች ይኖራሉ። በጥቅሉ ቃዶ ተብሎ የሚጠሩት እነዚህ የእምነቱ መሪዎች በቁጥር አራት ሲሆኑ፤ ከስራ ሐላፊነታቸው አንፃር ጋና፣ ቃሪቻ፣ ዎማ እና ጋዳላ ይባላሉ።

ከላይ እንዳነሳሁት የእምነቱን ተከታዮች ከፈጣሪ ወይም ከካሊቃ ጋር እንደድልድይ ሆኖ ያገናኛቸው የነበረው እና ያስተዳድራቸው የነበረው ሐላሌ ወደ ካሊቃ ከሄደ በሃላ ከፈጣሪ ጋር የማገናኘቱን ስራ ለአባቶች ስሰጥ ህዝቡን የማስተዳደር ስራ ሐላሌን ተክቶ እንዲሰሩ ከእምነቱ ተከታዮች መካከል ለተመረጡ ሰዎች ተሰጥቷል። ሐላፊነቱን የወሰዱት እነዚሁ ቃዶዎች ናቸው።

የእምነቱ ተከታዮች ከእምነቱ እና ከእለትለት ማህበራዊ ኑሮ ጋር በተገናኘ የሚገጥሟቸውን ችግሮች እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ መንፈሳዊ ማበረታቻዎችን እና ማህበራዊ ፍትሕ ለማግኘት ወደነዚህ ቅዱስ ቦታዎች በመሄድ ቃዶዎቹን ያገኟቸዋል። ቃዶዎቹም ሐላፊነት ከተቀበሉበት ጊዜ ጀምሮ ከቅዱስ ቦታዎቹን እየተንከባከቡ እድሜ ልካቸውን እዛው ይኖራሉ በምትካቸው ሌላ ቃዶ የሚመረጠው ሲሞቱ ብቻ ነው።

አራቱም የተለያየ የስራ ሐላፊነቶች ሲኖሯቸው፤ አንደኛው በሌላኛው ስራ ላይ ጠልቃ መግባት አይችሉም። ከዚህም በተጨማሪ እነርሱ በምሰጡት ውሳኔዎች ላይ ማንኛውም ውጫዊ አካል ጠልቃ መግባት አይችልም።

እንግዲህ የሲዳማ ባህላዊ ሐይማኖትን በተመለከተ በጣም በጥቂቱ ይህንን የሚመስል ሲሆን፤ ባህላዊ ሐይማኖቱ እንደሌሎቹ የዓለማችን ትላልቅ ሐይማኖቶች ሁሉ የራሱ የሆኑ ሕጎች ያሉት፣ የራሱ የሆነ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ያሉት፣ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት፣ የራሱ የሆነ ማምለኪያ ስፍራ ያለው እና በራሱ ሙሉ የሆነ ነው።የሲዳማ ባሕላዊ ሐይማኖት የኢትዮጵያ ብሔር ነው።