ዝም በል! ዝም በል!

ሽማግሌው የየካቲት ጊዮርጊስ ዕለት ታቦቱን ለማንገሥ፤ ሳይረፍድባቸው አቡሽን አስከትለው ወደጎረቤት አገር ይገሰግሳሉ። ታዲያ ዳገቱን ወጥተው ወደመረመሩ ሲያዘቀዝቁ እረኛ ልጃቸው ከቤት አንስቶ እየሮጠ ይከተላቸው ኖሮ፤ ትንፋሹ መለስ ሲልለት «አባባ! አባባ! ዶባን ሌባ ወሰደው» ይላቸዋል። በድንጋጤ ላብ የተዘፈቁት ሽማግሌ፤እግራቸው ከድቷቸው እተፈነገሉበት እንደተገሸሩ፤ «አዪ! የየለጡ ጊዮርጊስ እንደው የዛሬን ብለህ ዶባን ያስመለስክልኝ እንደሁ በሬ አገባልሃለሁ» ብለው ሲሳሉ ያዳመጣቸው አቡሽ፤ «አባዬ! ያለን በሬ አንድ ዶባ፤ እሱኑ ለጊዮርጊስ ካገባነው ለምኑ ነው!» ቢላቸው

«ዝም በል! ዝም በል! በሬው ይገኝ እንጂ ማን ይሰጠዋል ብለህ ነው።» አሉት ይባላል።